logo






የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ህዝቦች

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በቀደምት ነዋሪነት ወይም በስራ አጋጣሚ በርካታ የኢትዮጵያ ብሄሮችና ብሄረሰቦች ይገኛሉ፡፡ አንዱ ለሌላው ጉልበት፣ ውበት፣ ድምቀትና እውቀት ሆነው በልማት ጎዳና ተሰልፈዋል፡፡ ከነዚህ መካከል በክልሉ ቀደምት ነዋሪነት የሚታወቁት ጉሙዝ፣ በርታ፣ ሽናሻ፣ ማኦ እና ኮሞ የሚባሉ አምስት ብሄረሰቦች ናቸው፡፡ ውድ አንባቢዎች፣ ስለእነዚህ ነባር ብሄረሰቦች ምን ያህል ታውቃላችሁ? ትንሽ በትንሹ እንካችሁ፡፡

1.በርታ ብሄረሰብ

የበርታ ብሔረሰብ በምስራቃዊ ስናር/ሱዳን/ ግዛት የየገሪን የሚባለውን ተራራማ ሰፊ ግዛትና በኢትዮጵያ ውስጥ የአባይንና የዳቡስ ሸለቋማ አካባቢን ይዞ ለረጅም ጊዜ የኖረ ህዝብ ነው፡፡ ብሄረሰቡ ዛሬ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከሚገኙ አምስት ነባር ብሔረሰቦች አንዱ ሲሆን በአሶሳ ዞን ወረዳዎችና በበሎ ጅጋንፎይ ወረዳ በተለያየ ቦታ ሰፍሮ ይገኛል፡፡ በኢትዮጵያ ከሚገኙት ሶስት የቋንቋ ግንዶች (ሰመቲክ፣ ኦሞቲክና ናይሎ ሳሃራ) ውስጥ የበርታ ብሔረሰብ ቋንቋ በናይሎ ሳሃራ ውስጥ ይመደባል፡፡ አልፎ አልፎ ከሚስተዋሉት የባህላዊና የአምልኮ ስርዓቶች ውጪ አብዛኛው የበርታ ህዝብ የእስልምና እምነት ተከታይ ነው፡፡

18ኛው ክፍለ ዘመን የሲናሩ ፉኝ ግዛት በምስራቃዊ ሱዳን በኩል እስልምናን በቤኒሻንጉል ለማስፋፋት መነሳቱንና እምነቱ በበርታ ህዝብ ውስጥ መስረጽ መጀመሩ በታሪክ ይወሳል፡፡ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ በበርታ ህዝብ ቱፊታዊ ህላዊና ዓመታዊ በዓላቱ ላይ የእምነቱ ጥላ ጎልቶ ይታያል፡፡

በበርታ በማህበራዊና ባህል ስርዓታቸው ውስጥ የሚታወቁበት የእንግዳ አቀባበል ስርዓታቸው ነው፡፡ በርታዎች እንግዳን ይወዳሉ፡፡ ያከብራሉ፡፡ እንግዳው ከየትም ይምጣ ሁሉም ለማስተናገድ ዝግጁ ናቸው፡፡

የዘመናት ታሪክና ባህል ባለቤት የሆነው የበርታ ብሔረሰብ አካባቢው ባለው ወርቅ ሀብት ምክንያት ከጥንታዊ ግብፃዊያንና አክሱማዊያን ጋር ግንኙነት እንደ ነበረው የታሪክ መዛግብት ያወሳሉ፡፡ ለግብፅ ፈርኦኖች፣ ለአክሱምና ለመረዌ ነገስታት የባሪያና የወርቅ ንግድ ምንጭ በመሆን ግንኙነት እንደ ነበረው የታሪክ መዛግብት ሲያውሱ የሩቅ ዘመኑን ብቻ ሳይሆን የቅርብ ጊዜ ታሪካችን የመዘገበው ይህንኑም የክልሉን የወርቅ ሀብት ክምችት የሚያሳይ እውነታ ነው፡፡ ቀደም ሲል የበርታ ብሔረሰብ እንደ መካከለኛው የኢትዮጵያ ታሪክ በክልልና በቤተሰባዊ አገዛዝ ስር ነበር፡፡ ይህውም የሼህ ሆጀሌ አልሐሰን ቤተሰብ የአቆልዲ ወይም ከአሶሳ በስተደቡብ 15 ኪሎ ሜትር ላይ የሚገኝና አካባቢውን፣ አብዱረህማን ሆጄሌ ቤተሰብ መንጌና አካባቢዋን፣ የሙሐመድ መሐመድ ቤተሰብ ኮሞሻና አካባቢዋን እና ሙሐመድ አልሐሰን ቤተሰብ ባንባሺ ወይም ፋዲሺና አከባቢዋን ያስተዳድሩ ነበር፡፡ ከዚህ መካከል የሼህ ሆጄሌ ቀደምት የዘር ግንድ ዕቆህዲ በምትባለው ቦታ ላይ ሲሰፍር በተከታታይ ስድስት መሪዎች ነግሰው ነበር፡፡ እነሱም አቁራዊ፣ ኢማድ፣ አድጀዱ፣ ጉንባብ፣ እመድና አልሐሰን ነበሩ፡፡ ሸጎለን (አዲስ አበባ) ልብ ይሏል! እንደ ሌሎቹ ብሄረሰቦች የበርታ ብሄረሰብም የሚታወቅባቸው እሴት ጨማሪ ቅርሶችና ባህሎች አላቸው፡፡
  • ዙምባራ፡- በበርታ ብሔረሰብ ውስጥ በዋናነት የትንፋሽና የምት የሙዚቃ መሳሪያ፤ በዚህ የሚጨፈረው በደስታና በጥጋብ ወቅት እንደሆነ የባህሉ ባለቤቶች ይናገራሉ፡፡ መሳሪያዎቹ በተለያየ መጠን የተሰሩ ቁጥራቸው አስራ ሁለት ነው፡፡ የሙዚቃ መሳሪያው ዜማ የሚኖረውና ትርጉም የሚሰጠው አስራ ሁለት የመዝሙሩ ቡድን አባላት ሲሟሉለት ብቻ ነው፡፡ ሲጨፈር ጾታና እድሜ አይገደብም፡፡ የሚጨፈረው በደስታና በጥጋብ ወቅት እንደሆነ የባህሉ ባለቤቶች ይናገራሉ፡፡
  • የቤት አሰራር፡- አብዛኛዎቹ ሁለት ጎጆችን ይሰራሉ፡፡ ጎጆዎቹም አልሀልዋና ሹልጽጺዎ ይሏቸዋል፡፡ ሽንጺጺዎ የሴቶች መዋያና ዋና መኖሪያ ቤት ሲሆን ሴቶች ምግብን የሚያበስሉትም በዚሁ ቤት ውስጥ ነው፡፡
  • የበርታ ባህላዊና ማህበራዊ ህብረቶች፡- በደስታም ሆነ በሀዘን በእርሻም ሆነ በቤት ስራ በአንድ ሰው ጉልበት ሊሰራ የማይቻለውን ወይም አንድ ሰው ብቻውን ሊሰራው የማይችለውን ለማከናወን ባህላዊና ማህበራዊ ህብረቶች አሏቸው፡፡ የመረዳጃ ስርአታቸውም ሌላ ትኩረት የሚስብ ነው፡፡ አታምባ ወይም እቁብ በመባል ይጠራል፡፡ ብሔረሰቡ ውስጥ የሚተማመኑ ሰዎች ያለምንም የውል ሰነድ በቃል ብቻ ገንዘብን አዋጥተው የሚረዳዱበት ዘዴ ነው፡፡
  • የአመጋገብ ስርዓት፡- በርታዎች የአመጋገብ ስርዓታቸው በአብዛኛውን ተመሳሳይ ሲሆን ተወዳጅ ምግባቸው ገንፎ ነው፡፡ እንደዚሁም በቱርኮች እንደመጣ የሚነገረው "ቄንቄስ" /ባሚያና ዌካ/ በእንግሊዞች አጠራር ኦክራ የሚባለው ለወጥ መስሪያነት የሚያገለግል የአትክልት ዘር በብሔረሰቡ ዘንድ ከሁሉ የበለጠ ተወዳጅ ባህላዊ ምግብ ሆኗል፡፡ ቄንቄስ የሚሰራው ከስጋ፣ ከዓሳ፣ ከሽሮ ጋር ወይንም ብቻውን ተዘጋጅቶ ከገንፎ ጋር ወይንም በእንጀራ የሚበላ ነው፡፡ ከምግብነቱም ሌላ የመድሃኒትነት ፀባይ እንዳለው ይታመናል፡፡ ሳይበላሽ ለረዥም ጊዜ /እስከ 3 ዓመት/ መቆየት ይችላል፡፡
  • የአለባበስ ስርዓት፡- በበርታ አለባበስ ውስጥ ውብና ማራኪ የአለባበሶች የሚታዩት ጀላቢያ፣ ቶብ፣ መርከብ /ባለ ሾጣጣ አፍንጫ መጫሚያ/ እና አንገት ዙሪያ የሚጠለቀው ቫል የተባለ ስካርብ ሲለበሱ ነው፡፡ በባህሉ የሚዘወተሩ የልብስ ዓይነቶች በወንዶች ጀላቢያ እና በሴቶች ቶብ፣ ህጃብ /ሻርብ/ ናቸው፡፡ ጀላቢያ አብዛኛውን ጊዜ በበዓልና በሰርግ ላይ ይለበሳል፡፡ አልፎ አልፎ በአዘቦትና በሀይማኖታዊ ስፍራዎች ላይም ይለበሳል፡፡ ሴቶች ቶብን ጠምጥመውና ፊትን በማይከልል መልኩ በህጃብ ፀጉራቸውን በመሸፈን ይለብሳሉ፡፡
  • የጋብቻ ሁኔታ፡- በህዝቡ ዘንድ ጎልቶ የሚታወቁ ሁለት የጋብቻ አይነቶች አሉ፡፡ እነሱም የውርስና የስምምነት የጥሎሽ /የኒካ/ የሳደቅ ጋብቻ ናቸው፡፡ በብሔረሰቡ ዘንድ ለክብረ ንጽህና ከፍተኛ ግምት ይሰጣል፡፡ ክብረ ንጽህናዋን ያልጠበቀች ከሆነች በዚያው ቀን ሊፋቱ ይችላሉ፡፡ አብዛኛውን ጊዜ የጋብቻ ስርዓት የሚካሄደው ከእህል ወቂያና መከር በኋላ ክረምት መግቢያ ድረስ ነው፡፡

2.ጉሙዝ

ጉሙዝ የሚለው የአማርኛ መጠሪያ በብሄረሰቡ ቋንቋ "ጉንዛ" ከሚለው ቃል የተወሰደ ሲሆን ፍችውም ጀግና ፣ ጎበዝ ፣ ወንድ እንደማለት ነው፡፡ ከናይሎቲክ የዘር ግንድ የሚመደቡትን የጉሙዝ ብሄረሰብ ጥንተ-መኖሪያ አስመልክቶ በርካታ መላምቶች ቢኖሩም በምዕራቡ የሃገራችን ክፍል ይኖሩ ነበር የሚለው ግን ባብዛኛው የብሄረሰቡ ዓባላት ዘንድ ተቀባይነት አለው፡፡ (አድማሱ ተክሌ) ብሄረሰቡ በጋራ የመኖር ፣ በጋራ የመሥራት ፣ በጋራ የመብላትና በጋራ የመጠጣት አኩሪና አስደሳች ማኅበራዊ ህይወትን የታደለ ነው፡፡ ብሄረሰቡ እጅጉን አስደማሚ ባህል ፣ በእጅጉ ማራኪ ታሪክና በጣሙንም መሳጭ መንፈሳዊና ቁሳዊ ቅርሶች አሉት፡፡ ከእነዚህ መካከል፡-  ዴሞክራሲያዊ የምርጫና አስተዳደር ሥርዓት  ቆሚያ (ባህላዊ የትንፋሽ የሙዚቃ መሳሪያ)፡- ከተመረጡ የዛፍ አይነቶች የሚሰራና ሁነቶችን ወይም ከረስተቶችን ምክንያት አድርጎ የሚነፋ ነው፡፡ ምሳሌ፡- የብሄረሰቡ ታላቅ ሰው ወይም የሀይማኖት መሪ ሲሞት፣ የተዘራ ሰብል ደርሶ ወደ ጎተራ ሲገባ፣ በዘመን መለወጫና በክብረ በዓላት ወቅት፣ ወ.ዘ.ተ.  ኤፂፃ (በሴቶች እግር ላይ የሚታሰርና ለዘፈን ማድመቂያነት የሚያገለግል ባህላዊ የሙዚቃ መሳሪያ)፡- ሴቶቹ እግራቸውን በማንሳት በለመዱት ስልት ደጋግመው መሬቱን ሲመቱ እርስ በእርሱ እየተጋጨ “ክሽ ክሽ ክሽ፣ ክሽ” የሚል ማራኪ ድምጽ ያሰማል::  ሲያያ (የቤት ውስጥና ውጪ መገልገያ እቃ አይነት)፡- ሴቶች በግራና በቀኝ ትከሻቸው ወይም አንዱ ላይ በማሳረፍ እንደ ሚዛን የሚጠቀሙበት ከገመድና ከእንጨት የሚዘጋጅ የዕቃ መሸከሚያ ነው፡፡)  ቀስት፡- ለአደንና ጠላትን ለመከላከል የሚጠቀሙበት ድምጽ አልባ መሳሪያ

3. ሽናሻ

ሽናሻዎች አንዳንዴ ቦሮ ሽናሻ በመባል ይጠራሉ፡፡ የሺናሻ ብሄረሰብ ዓባላት ጥንተ መኖሪያ ምድረ እስራኤል፣ የዘር ግንዳቸውም ከነገደ ከነዓን እንደሆነ እና በ3 ሺህ 679 ዓ.ዓ አካባቢ ወደ ኢትዮጵያ እንደገቡ ይነገራል (አለቃ ታዬ ÷የኢትዮጵያ ህዝብ ታሪክ) ፡፡ ወደ ኢትዮጵያ እንደገቡ በተለያዩ የሃገሪቱ አካባቢዎች በተለይም በዓባይ ወንዝ ወዲያና ወዲህ ማዶ መኖር እንደጀመሩ የጽሁፍና የአፈታሪክ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ “ሺናሻ” የሚለው ስያሜ የተሰጣቸው ወደ ኢትዮጵያ በተለይም ወደ ደቡብ ጎጃም ሲገቡ በርካታ ሺዎች ሆነው ስለነበር ይህን የህዝብ ጎርፍ የተመለከቱ የአካባቢው ኗሪዎች “ሺ እና ሺ ሰዎች” “Thousands & Thousands of people” መጡ በማለት ከተናገሩት የመነጨ እንደሆነ እኒሁ ተመራማሪ ፕላዚኮስኪ እና ብራውነር የተሰኙ የዘርፉ ተመራማሪዎች አለቃ ታዬ የተባሉ የሃገራችንን ምሁር በመጥቀስ እንደጻፉ ይናገራሉ፡፡ (አሠፋ÷ገፅ÷59) አሁን አሁን ደግሞ ሺናሻ የሚለው መጠሪያ ምንጭ ከፍ ሲል የተባለው ሳይሆን “ሺኒ አሻ” ከሚል የሺናሺኛ ቃል የተወሰደ ነው የሚሉ ተከራካሪዎችም እየተስተዋሉ ነው፡፡ “ሺኒ” ማለት የመጀመሪያ ወይም ቀደምት “አሻ” ማለት ደግሞ ህዝብ ማለት በመሆኑ በጥቅሉ ቀደምት ህዝብ ማለት ነው ሲሉ ያስረዳሉ፡፡ “የከነዓን ልጆች የመጀመሪያ ህዝብ” የሚለው“ ሚዛን የሚደፋ ሆኖ ይታያል” በማለት የቋንቋ ምሁር የሆኑት አድማሱ ተክሌ ምክንያታቸውን የአናባቢና ተነባቢ ተጽዕኖ በመጥቀስ ያስረዳሉ፡፡ ክርክሩን ለጥናትና ምርምር እንተው፡፡ በማህበራዊ ኑሮ ረገድ የብሔረሰቡ አባላት የጠበቀ የእርስ በርእስ ግንኙነት ያላቸው ሲሆን፡-  በበአል ቀናት ሞቅ ያለ ድግስ በማዘጋጀት (ጭምቦ የተሰኘ ባህላዊ ምግብና ቦርዴ የተባለ ጠላ ተጠምቆ) ተሰባስበው በመብላት ፣ በመጠጣት ፣ በመዝፈን ፣ በመጨፈር ፣ በመወያየትና በመመራረቅ ይዝናናሉ፡፡  በእርሻና በቤት ሥራ (ጎጆ ቅለሳ) ወቅትም በ”ደቦ” (በሺናሽኛ ዊዳ ይሰኛል) መልክ በመተባበር ሥራቸውን ያቀላጥፋሉ፡፡  የሠርግና የለቅሶ ሥርዓቶቻቸውም የብሕረሰቡን ወግና ልማድ ተላብሰው ከሚከናወኑት በርካታ የማንነት መገለጫ እሴቶቻው ጥቂቶቹ ናቸው  የብሔረሰቡ አባላት ባህላዊ የዳኝነት ሥርዓታቸውም የአይጣሴነት ባህርይ አለው፡፡  የሴቶች የፀጉር አሰራር (ሽሩባ) ውበት አለው፡፡  ስርቆት፣ መዋሸት፣ የሰውን ሀብትና ንብረት አጭበርብሮ መጠቀም ወይም ለጥቅም ሲባል አንዱን ሰበብ ፈጥሮ ማፈናቀል፣ ነፍስ ማጥፋት፣ የስጋ ዝምድና ካለው ሰው ጋር ትዳር መመስረት በብሄረሰቡ ክፉኛ ይወገዛል፣ አድራጊው ይረገማል፡፡

4. ማኦ ብሄረሰብ

የማኦ ብሄረሰብ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግስት ነባር ከሚባሉት አምስት ብሄረሰቦች መካከል አንዱ ነው፡፡ ብሄረሰቡ በዋናነት የሚታወቀው ከክልሉ በስተደቡብ ኦሮሚያ ክልልና ሱዳን በሚያዋስኑት በማኦ ኮሞ ልዩ ወረዳ ውስጥ ነው፡፡ ከወረዳው ውስጥ በብዛት የሚኖሩትም ሽጎጎና ገዳሾላ በሚባሉ ቀበሌዎች ውስጥ ሲሆን ከነዚህ ቀበሌዎች ውጪም ጫንጋላ፣ ፓሽማ፣ ውስኩ፣ ሸንታ፣ ጎባና ቤልዲግስ አከባቢዎች ላይ በተለያየ አሰፋፈር ይኖራሉ፡፡ ከማኦ ኮሞ ልዩ ወረዳ ውጪም አጎራባች ወረዳ በሆነው ባምባሲ፣ በኦሮሚያ ክልል፣ በጋምቤላ ክልል፣ በሱዳን ድንበር አከባቢ የተለያዩ ቦታዎች ሰፍረው እንደሚገኙ የብሄረሰቡ ሽማግሌዎችና የጽሁፍ መረጃዎች ያስረዳሉ፡፡ የማኦ ብሄረሰብ የራሱ የሆነ ማህበራዊ ክንዋኔዎች፣ ስነስርዓቶችና ፌስቲባሎች፣ የተፈጥሮ እውቀትና ትግበራዎች፣ ትውፊታዊ የእደ ጥበብ እውቀቶችና ክህሎቶች እንዲሁም ሀገረሰባዊ ትውን ጥበባት አሉት፡፡ ከነዚህ ውስጥ  የጋብቻ ክንዋኔና የሰርግ ዘፈኖች፣  የሴቶች የጨሌና የነሀስ ጌጣጌጦች፡- የጨሌዎቹ ጅምላ መጠሪያ “ጺል” ሲባል ለየአካል ክፍል ሲሆን ግን የተለያየ መጠሪያ ይኖረዋል፡፡ በአፍንጫ፣ በጆሮዋ፣ በጡንቻ፣ በክንድ፣ በአንገትና በወገብ(በዳለ) ይለበሳል፤  ንብ የማነብ እውቀትና ትግበራ፣  እንግዳ አቀባበል፣  የብረት ስራ እደጥበብ እውቀቶችና ክህሎቶች ጥቂቶቹ ናቸው፡፡

5. ኮሞ ብሔረሰብ

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከሚገኙት አምስት ነባር ብሔረሰቦች ውስጥ አንዱ የኮሞ ብሔረሰብ ነው፡፡ ብሔረሰቡ በክልሉ በስተደቡብ አቅጣጫ በማኦ ኮሞ ልዩ ወረዳ የሚገኝ ሲሆን ከክልሉ ውጭ ደግሞ በጋምቤላ ክልልና በሱዳን ሀገር በተለይም በደቡብ ሱዳን ከኢትዮጵያ ኩታገጠም በሆነው ሥፍራ ይገኛል፡፡ ቋንቋቸውም አንድ ዓይነት፣ ባህላቸውና የአመጋገብ ሥርዓታቸው ተመሳሳይ ነው፡፡ ኮሞ የብሔረሰቡ መጠሪያ ሲሆን ቋንቋው ኮማ ወይም ዲኒ (koma or Dine) ይባላል፡፡ የቋንቋው ቤተሰብ በሀገራችን ከሚነገሩት አራት የእናት ቋንቋ ምድቦች በአብዛኛው በምዕራብና በደቡብ ኢትዮጵያ ጠረፋማ ሥፍራዎች የሚገኙት ቋንቋዎች ማለትም የማኦ ፣ የመዠንግር ፣ የኑዌርና ወዘተ. እናት ቋንቋ ነው ተብሎ የሚነገረው ኒሎሳሃራ (Nilo-Saharanlanguage family) ነው፡፡ ብዙዎቹ የብሔረሰቡ አባላት ጓዋማ (Guwama-የማኦ ቋንቋ)፣ ኦሮምኛና አረብኛ ቋንቋን ያቀላጥፉታል፡፡ ለዚህ በምክንያትነት የሚጠቀሰው አብረው መኖራቸውና ሰፊ የሆነ ማኅበራዊ ግንኙነት ያላቸው መሆኑ ነው፡፡ የኮሞ ብሔረሰብ ተነግረው የማያልቁ ሀገር ጎብኝዎችን የሚማርኩ፣ ጥናትና ምርምር አድራጊዎችን የሚስቡ፣ ኪነጥበብ ባለሙያዎችን የሚያማልሉ፡፡ ያልተበረዙና ያልተከለሱ፣የዘመኑ ባህል ወረራ ያልተጠናወታቸው፣ ውበታቸው ያልደበዘዘ፣ በእምነትና በጽናት ማኅተም የታተሙ አያሌ ባህሎች አለው፡፡ ይህን ግምት ውስጥ በማስገባት ይመስላል ለሶስተኛ ድግሪ ማሟያ ጥናት የሚሰሩ ተማሪዎች፣ ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል፣ የውጪ ዜጎች ወዘተ. ወደሥፍራው መትመም ጀምረዋል፡፡ ዓባይን በጭልፋ እንዲሉ ጥቂቶቹን ለማስታወስ ያህልም  የእንግዳ አቀባበላቸውንና አክብሮታቸውን፣  ባህላዊ ጭፈራቸውን፣ ባህላዊ ሕክምናቸውን፣  የጨቅላ ሕጻናትና ወላድ እናትን እንዲሁም የዕድሜ ባለፀጎች (አዛውንቶች) አያያዛቸውን፣  የሴቶችና ወጣት ወንዶች መዋቢያ ጌጣጌጦች (ጨሌ) አሠራራቸውንና በሚሰሯቸው መዋቢያዎች ሲዋቡ፣  የድምፅና የትንፋሽ ባሕላዊ ሙዚቃ መሳሪያቸውን፣ ሆንተብሎ ሰው መግደልእንደሌለና ካጋጠመም በኮሞዎች ዘንድ አስነዋሪነቱን፣  የባሕላዊ እርቅ ሥርዓቱን፣ሬሳ ሳይበላሽ/ሳይሸት ለረጅም ጊዜ ማቆየት መቻልን፣  የአፋዊ ትውን ጥበባት (Oral literature)፣  በአካባቢያቸው ያለው የተፈጥሮ ሀብት ስብጥሩንና እድሜ ጠገብ ሀገር በቀል ዝርያዎች በብዛት መኖራቸውን ልብ ይሏል፡፡ ብሔረሰቡ በተፈጥሮ ደግ ሩኅሩኅና በኅብረት የሚኖር ከመሆኑም ሌላ ከራሱ ከብሔረሰቡ አልፎ በቅርብ አብረው ከሚኖሩትና አንድን ወረዳ በማዕከላዊነት ከሚጋሩት ማኦዎች ጋር በእጅጉ ተቀራርበውና ተሳስበው ይኖራሉ፡፡ ሁለቱም ብሔረሰቦች የየራሳቸው የሆነ ቋንቋ፣ባህል፣ወግና ሥርዓት ያላቸው ሲሆን የሚጋሯቸው በርካታ ዕሴቶች አሉ፡፡ ለአብነት ያህልም አንደኛው የሌላኛውን ቋንቋ መናገር መቻል እና ከአንድ በላይ ቋንቋ መቻል፣በጋብቻ መተሳሰር፣ በእንግዳ አቀባበል ባህል፣ በአለባበስና የአኗኗር ዘይቤ፣ የአደንና የእርሻ ሥራ ተመሳሳይነት ሊጠቀሱይችላሉ፡፡ ከዚህም ሌላ በአካባቢያቸው ካሉት በርታዎችና ኦሮሞዎች ጋር ብዙ ቅርበት አላቸው፡፡ የክልሉ አስተዳደራዊ መዋቅርን በሚመለከት ክልሉ በሶስት ዞኖች፣ሃያ አንድ ወረዳና አንድ ልዩ ወረዳ የተከፈለነው፡፡ ዞን አሶሳ፣መተከልና ካማሽ ናቸው ልዩ ወረዳ፡- ማኦ እና ኮሞ ወረዳዎች፡- አሶሳ፣ሆሞሻ፣መንጌ፣ሸርቆሌ፣ኩርሙክ፣ባምባሲ፣ኦዳቢልድግሉ፣ካማሽ፣ አጋሎሜጢ፣ያሶ፣ሰዳል፣በሎ ጅጋንፎይ፣ማንዱራ፣ዲባጢ፣ቡለን፣መንበራ፣ፓዌ፣ዳንጉር፣ጉባ ናቸው የሕዝብ ብዛት ወንድ 512,004 (50.8%) ሴት 517,000 (49.2%) ድምር 1,035,000(አንድ ሚሊየን ሰላሳ አምስት ሺህ)