logo

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሁሉም ወረዳዎች አንፃራዊ ሰላም ማስፈን መቻሉን ርዕስ መስተዳድር ክቡር አቶ አሻድሊ ሀሰን ገለፁ፡፡

መንግስት ባደረገው ያላሰለሰ የሰላም ጥረት በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሁሉም ወረዳዎች አንፃራዊ ሰላም ማስፈን መቻሉን ርዕስ መስተዳድር ክቡር አቶ አሻድሊ ሀሰን ገለፁ፡፡ የክልሉ መንግስት ባደረገው ያላሰለሰ የሰላም ጥረት በክልሉ ሁሉም ወረዳዎች አንፃራዊ ሰላም ማስፈን መቻሉን ርዕስ መስተዳድር ክቡር አቶ አሻድሊ ሀሰን በምክር ቤቱ 18ኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ ገልፀዋል ፡፡ የሰላም እጦቱ እንዳይደገም አሁንም ጥረቱ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ርዕሰ መስተዳድሩ አስታውቀዋል፡፡ ርዕስ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን ለክልሉ ምክር ቤት 18ኛ መደበኛ ጉባኤ ባቀረቡት የ2016 ሪፖርት የተጀመሩ የልማት ስራዎች ዘላቂነታቸውን ለማረጋገጥ በዋናነት በከፍተኛ መስዋእትነት የተገኘውን ሰላም የበለጠ ማፅናት እንደሚገባ አሳስበዋል። ሰላሙ ህዝባዊ መሰረት እንዲይዝ ማድረግና ዘላቂነቱን በአስተማማኝ ሁኔታ ማረጋገጥ ትኩረት ተሰቶት እየተሰራ ያለ ጉዳይ መሆኑንም ገልፀዋል፡፡ ርዕሰ መስተዳድሩ አክለውም የሰላም እጦት በዜጎች ህይወት እና በሀገር ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ እና የከፋ ችግር ማስከተሉን አስታውሰው ይህንን ለማስተካከል ባለፉት አመታት በሀገር፣ በተለይ ደግሞ በክልሉ የደረሰውን ሁኔታ መለስ ብሎ ማየት ይገባልም ሲሉ ተናግረዋል፡፡ ችግሮቹን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የክልሉ መንግስት ረጅም ርቀት መጓዙን ያብራሩት አቶ አሻድሊ ሀሰን፤ ጠቅላይ ሚንስትሩን ጨምሮ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዋች እና የመከላከያ ጀነራል መኮንኖች በተገኙበት ተደጋጋሚ ውይይቶችን በማካሄድ የችግሩን መንስኤ ለማወቅ ከፍተኛ ጥረቶች መደረጋቸውንም ነው ያብራሩት፡፡ የክልሉ መንግስት እስከ ሱዳን በመሄድ የሰላም ስምምነቶችን መፈራረሙን የጠቀሱት ርዕስ መስተዳድሩ ለሰላሙ ሲባል በክስ ሂደት ላይ የነበሩ ተጠርጣሪዎችንም ክሳቸው እንዲቋረጥ ተደርጎል ብለዋል፡፡ በተለያዩ ጊዜያት በባህልና በእምነት የታገዘ የእርቅና የይቅርታ መድረኮችን በማዘጋጀት በህዝቦች መሀከል የቀድሞ ወንድማማችነት እና ኢትዮጵያዊ አብሮነት ስሜት እንዲመለስ ከፍተኛ ጥረት በማድረግ በክልሉ አንፃራዊ ሰላም እንዲሰፍን ማድረግ ተችሎል ሲሉ ተናግረዋል ፡፡ የሰላም ጉዳይ የህልውና ጉዳይ ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ይህንን ሰላም በዘላቂነት ማፅናት፣ ህዝባዊ መሰረት እንዲይዝ ማድረግና ዘላቂነቱን በአስተማማኝ ሁኔታ ማረጋገጥ የሁሉም ምክር ቤት አባላት ሀላፊነት መሆን አለበት ሲሉም አሳስበዋል፡፡ የሰላም ተመላሾች ከህዝቡ ጋር ተቀላቅለው በሰላም መኖር እንዲችሉ ተከታታይነት ያለው የተሃድሶ ስልጠና እንዲወስዱ ከመደረጉ ባሻገር በመረጡት የስራ ዘርፍ በማሰማራት ከራሳቸው ባለፈ በክልሉ ኢኮኖሚ ግንባታ ሂደት ውስጥ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ለማስቻል የተለያዩ ድጋፎች እየተደረገላቸው መሆኑንም ርዕስ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ገልጸዋል።

Image

አስተያየት ይስጡ

Comments