logo

እንደ ሀገር የተጀመረውን የፍትህ ትራንስፎርሜሽን ፍኖተ ካርታ ከግብ ለማድረስ እየተሰራ ያለው ጅምር ሥራ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት የክልሉ ምክር ቤት አባላት ገለፁ።

(የካቲት፣12/2016 ዓ.ም) እንደ ሀገር የተጀመረውን የ3 ዓመት የፍትህ ትራንስፎርሜሽን ፍኖተ ካርታ በክልሉ ከግብ ለማድረስ እየተሰራ ያለው ጅምር ሥራ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት አባላት ገልፀዋል። የክልሉ ምክር ቤት አባላት በክልሉ የቀጣይ ሶስት ዓመት የፍትህ ትራንስፎርሜሽን ፍኖተ ካርታ ዙሪያ ላይ ውይይት አድርገዋል። የምክር ቤት አባላቱ በክልሉ የፍትህ ዘርፍ የትራንስፎርሜሽን እቅድን ለመፈፀም እየተደረገ ያለው ጥረት የክልሉን የህብረተሰብ የፍትህ ጥያቄ ፈጣን፣ ቀልጣፋና ውጤታማ የሆነ አገልግሎት ለመስጠት፤ለመፍታትና በፍትህ ዘርፉ ላይ መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣት የተጀመሩ ጥረቶች መልካም በመሆናቸው ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው ብለዋል። ከማህበረሰቡ ለሚነሳው የፍትህ ጥያቄ ትክክለኛውን የፍትህ ተደራሽ ለማድረግ ለሥራው የሚያግዙ ተቋሙን በሰው ሀይል እና በቴክኖሎጂ ከማደራጀት አንፃር ትኩረት ሰጥቶ መሠራት እንዳለበትም የምክር ቤቱ አባላት አሳስቧል። በውይይት መድረኩ ላይ የተገኙት የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት አፈጉባኤ ክቡር ዶ/ር ተመስገን ዲሳሳ በክልሉ የተጀመረውን የፍትህ ተቋማት ትራንስፎርሜሽን ውጤታማነት የምክር ቤቱ አባላት እገዛ እና ድጋፍ ያስፈልጋል ብለዋል። የፍትህ ትራንፎርሜሽኑን ዕቅድ ውጤት ላይ ለማድረስ የፍርድ ቤት እና የፍትህ ተቋማት ከተለምዷዊ አሰራር መውጣት እንዳለባቸውም ክቡር አፈጉባኤው አሳስበዋል። የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ክቡር አቶ ሠንበታ ቀጀላ በበኩላቸው የለዉጥ ፍኖተ ካርታው ዋነኛ ግብ የተገልጋዩን ህብረተሰብ የዳኝነት አገልግሎት ፍላጎት መሆኑን ገልፀዉ የለዉጥ ሥራዉ የህብረተሰቡን ጥያቄዎችና ፍላጎቶች ማዕከል ያደረገ መፍትሔ ሰጪ ሊሆን እንደሚገባም አስገንዝበዋል። ፕሬዝዳንቱ አክለዉም የህብረተሰቡን የፍትህ ጥማት ለማርካት እና ህብረተሰቡ ለሚጠይቀዉ የዳኝነት አገልግሎት ጥያቄ ተገቢና ትክክለኛ ምላሽ ለመስጠት የዳኝነት ሥራዎችን ማዘመን ተገቢ ነው ብለዋል። የወንጀል፣የፍትሐ-ብሔር እና የአስተዳደር ህግን በልዩ ሁኔታ ማየት፣ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም፣ ምቹ የሥራ ሁኔታ እና ቅንጅታዊ አሰራር ማስፈን ፍኖተ ካርታው ካካተታቸው ነጥቦች መካከል እንደሚገኙበት ለምክር ቤቱ አባላት በቀረበው የውይይት ሰነድ ላይ ተመላክቷል።

Image

አስተያየት ይስጡ

Comments